ይህ አዲስ መመሪያ ከቅድመ ወሊድ ምርመራ ጀምሮ እስከ ወሊድ ድረስ ያሉ ማናቸውንም የህክምና አገልግሎቶች ያካተተ ሲሆን ወላጆች ከኪሳቸው ምንም አይነት ክፍያ እንዳይከፍሉ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ቻይና በአሁኑ ወቅት የ1.416 ቢሊዮን ህዝብ ባለቤት ብትሆንም በህዝብ ብዛት በህንድ ተበልጣ የዓለማችን ሁለተኛዋ ሀገር ሆና ትገኛለች። የሀገሪቱ የህዝብ ቁጥር ከ2022 ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ማሽቆልቆል የጀመረ ሲሆን ይህ አዝማሚያ እስከ 2025 ድረስ ቀጥሎ ታይቷል።
ለዚህ የህዝብ ቁጥር መቀነስ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ተብለው የሚጠቀሱት ለበርካታ አስርት ዓመታት ተግባራዊ የነበረው የአንድ ልጅ ብቻ ፖሊሲ፣ የከተማ መስፋፋት እና የልጆች ማሳደጊያ ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ መናር ናቸው።
መንግስት የወሊድ ወጪን ሙሉ በሙሉ በነጻ ለማድረግ የወሰነውን እርምጃ ተከትሎም ከጃንዋሪ 2026 ጀምሮ በእርግዝና መከላከያ ቁሶች ላይ የ13 በመቶ ታክስ ለመጣል ማቀዱ ተሰምቷል።
ቤጂንግ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈችው ወደፊት ሊያጋጥማት የሚችለውን የሰው ኃይል እጥረት ለመከላከል እና የኢኮኖሚ ጥንካሬዋን ለማስቀጠል እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ።