ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው ወቅት አሜሪካ በግድቡ የድርድር ሂደትና በገንዘብ ድጋፍ ዙሪያ ያላትን ሚና በተመለከተ የተናገሯቸው ነጥቦች ከሀቁ ጋር እንደሚጋጩ ተመልክቷል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመግለጫቸው ወቅት "ናይል ለግብፅ እጅግ አስፈላጊ ነው" ካሉ በኋላ፣ አሜሪካ ለግድቡ ግንባታ ፋይናንስ ማድረጓን የሚጠቁም ንግግር አድርገዋል። ፕሬዝዳንቱ "እንዴት እንዲህ እንዲሆን (ግንባታው እንዲቀጥል) ፈቀድን?" በማለት የጠየቁ ሲሆን፣ ይህም አሜሪካ በግድቡ ግንባታ ላይ ቀጥተኛ የገንዘብ ተሳትፎ እንዳላት የሚያስመስል ነበር። ይሁን እንጂ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕዝቡ የሀገር ውስጥ ፋይናንስ የተሸፈነ መሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ሀቅ ነው።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ሊፈጠር ይችል የነበረውን ግጭት በመካከለኛነት በመግባት እንዳስቀሩት ገልጸዋል። "ጦርነት እንዳይነሳ አድርጌያለሁ" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ አሁንም በጉዳዩ ላይ መፍትሄ ለመፈለግ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል። ትራምፕ ለግብፅ ያላቸውን ወገንተኝነት በንግግራቸው ውስጥ በግልጽ ያሳዩ ሲሆን፣ "ናይል ሲባል የማውቀው ግብፅን ነው" በማለት የገለጹት አባባል የወንዙ ዋነኛ ምንጭ የሆነችውን ኢትዮጵያን ጥቅም ያላገናዘበ ነው በሚል በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቃውሞ እያስነሳ ይገኛል።
ይህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር በኢትዮጵያ በኩል የታሪክና የሀቅ ስህተቶች እንዳሉበት እየተገለጸ ነው። በተለይም የግድቡ ፋይናንስ ምንጭን በተመለከተ የተነገረው የተሳሳተ መረጃ እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መብት ያላከበረ አቀራረብ በሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ይገምታሉ። መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን ይፋዊ ምላሽ ባይሰጥም፣ በማህበራዊ ሚዲያ የሚንጸባረቁ አስተያየቶች ግን ንግግሩ ሀቁን ያልተከተለ መሆኑን እያመለከቱ ነው።
ትላንት የግብፅ የውሃ ሚኒስትር ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ምክንያት ለደረሰ የውሃ እጥረት ለግብፅና ለሱዳን ካሳ መክፈል እንዳለባት መጠየቃቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የዛሬው የፕሬዝዳንት ትራምፕ መግለጫም ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ለምታደርገው ለዚህ መሰሉ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ተጨማሪ ግብዓት ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል።